53:1የሰማነውን ነገር ማን አመነ?
የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?
2በፊቱ እንደ ቡቃያ፣
ከደረቅም መሬት እንደ ወጣ ሥር በቀለ፤
የሚስብ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤
እንድንወደውም የሚያደርግ መልክ አልነበረውም።
3በሰዎች የተናቀና የተጠላ፣
የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር።
ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት፣
የተናቀ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም።
4በርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤
ሕመማችንንም ተሸከመ፤
እኛ ግን በእግዚአብሔር እንደ ተመታ፣
እንደ ተቀሠፈ፣ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው።
5ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤
ስለ በደላችንም ደቀቀ፤
በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤
በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።
6እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤
እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጐድን፤
እግዚአብሔርም፣ የሁላችንን በደል
በእርሱ ላይ ጫነው።
7ተጨነቀ፤ ተሠቃየም፤
ነገር ግን አፉን አልከፈተም፤
እንደ ጠቦትም ለዕርድ ተነዳ፤
በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣
አፉን አልከፈተም።
8በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤
ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ተመቶ፣
ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ፣
ከትውልዱ ማን አስተዋለ?
9በአፉ ተንኰል ሳይገኝበት፣
ምንም ወንጀል ሳይሠራ፣
አሟሟቱ ከክፉዎች፣
መቃብሩም ከባለጠጎች ጋር ሆነ።
10መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤
እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣
ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤
የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።
11ከነፍሱ ሥቃይ በኋላ፣
የሕይወት ብርሃን ያያል፤ ደስም ይለዋል፤
ጻድቅ ባሪያዬ በዕውቀቱ ብዙዎቹን ያጸድቃል፤
መተላለፋቸውንም ይሸከማል።
12ስለዚህ ድርሻውን ከታላላቆች ጋር እሰጠዋለሁ፤
ምርኮውን ከኀያላን ጋር ይካፈላል፤
እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ፣
ከክፉ አድራጊዎችም ጋር በመቈጠሩ፣
የብዙዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤
ስለ ዐመፀኞችም ማለደ።
ደረጃ 2፡ ታሪኩን እንደገና ይናገሩ
ታሪኩን በራስዎ ቃል ለመድገም ጥቂት ጊዜ ይውሰዱ። ጮክ ብለህ መናገር ወይም መጻፍ ትፈልግ ይሆናል። ለማስታወስ እየታገልክ ከሆነ እንደገና አንብብ ወይም አድምጠው።
ደረጃ 3፡ ታሪኩን አግኝ
ታሪኩን በደንብ እንደምታውቀው ሲሰማህ ለማሰብ ጊዜ ውሰድ ወይም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ
- ይህ ታሪክ ስለ እግዚአብሔር ምን ይነግርሃል?
- ይህ ታሪክ ስለ ሰዎች ምን ይነግርሃል?
- ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ቃል ከሆነ በሕይወትህ ውስጥ ምን ለውጦችን ማድረግ ይኖርብሃል?
- ለማን ትናገራለህ?
Get Discovery Bible Studies on your phone
Discover copyright ©2015-2026 discoverapp.org
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የቅጂ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.® ፍቃድ የተሰጠው በ Biblica, Inc.®። መብቱ በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version (Addisu Medebegna Tirgum) Copyright © 2001 by Biblica, Inc.® Used by permission of Biblica, Inc.® All rights reserved worldwide.