
የሚከተለውን ክፍል ያንብቡ ወይም ያዳምጡ
9:35ኢየሱስ በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች እየሰበከ እንዲሁም ደዌንና ሕመምን ሁሉ እየፈወሰ በከተሞቹና በመንደሮቹ ዞረ። 36ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው። 37ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ 38ስለዚህ የመከሩ ጌታ፣ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት።”
10:1ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ ርኵሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፣ ደዌንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው።
2የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም የሚከተለው ነው፦ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣ 3ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ፣ 4ቀነናዊው ስምዖንና በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮቱ ይሁዳ።
5እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ እንዲህ ከሚል ትእዛዝ ጋር ላካቸው፤ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ። 6ይልቁንስ የእስራኤል ቤት ወደሆኑት ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ። 7ሄዳችሁም፣ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ። 8በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ። 9በመቀነታችሁ ወርቅም ሆነ ብር ወይም መዳብ አትያዙ። 10ለመንገዳችሁም ከረጢት፣ ትርፍ እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ የዕለት ጕርሱ ይገባዋልና።
11 “ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጋችሁ በቤቱ ዕረፉ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያው ቈዩ። 12ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ። 13ቤቱም የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስላችሁ። 14ማንም ሰው ሊያስተናግዳችሁ ወይም የምትናገሩትን ሊሰማ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ከቤቱ ወይም ከከተማው ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ። 15እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን በዚያች ከተማ ከሚደርሰው ቅጣት ይልቅ በሰዶምና በገሞራ የሚደርሰው ይቀላል።
16 “እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ።
ታሪኩን በራስዎ ቃል ለመድገም ጥቂት ጊዜ ይውሰዱ። ጮክ ብለህ መናገር ወይም መጻፍ ትፈልግ ይሆናል። ለማስታወስ እየታገልክ ከሆነ እንደገና አንብብ ወይም አድምጠው።
ታሪኩን በደንብ እንደምታውቀው ሲሰማህ ለማሰብ ጊዜ ውሰድ ወይም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ
Get Discovery Bible Studies on your phone
Discover copyright ©2015-2026 discoverapp.org
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የቅጂ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.® ፍቃድ የተሰጠው በ Biblica, Inc.®። መብቱ በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version (Addisu Medebegna Tirgum) Copyright © 2001 by Biblica, Inc.® Used by permission of Biblica, Inc.® All rights reserved worldwide.